ልደቱ አያሌው
ታህሳስ 16፤ 2016 ዓም
“መንግሥትም በዙሪያው ለሰበሰባቸው አድርባዮች ያስለመደውን ጥቅም ማከፋፈል፣ በስሩ ለሚገኘው ሰራተኛ ደመወዝ መክፈል፣ ለሠራዊቱም ስንቅና ትጥቅ የማቅረብ አቅም ያጣል። ስርዓት አልበኝነትና ሙስናም በከፍተኛ መጠን ይባባሳል። በሂደትም ማዕከላዊ መንግሥቱ ይዳከማል፣ አብዛኛው የአገሪቱ ግዛትም በተለያዩ ታጣቂ ኃይሎችና የጎበዝ አለቆች እጅ ይወድቃል። መንግስትም ግብርና ቀረጥ ከሕዝብ መሰብሰብ የማይችልበት ሁኔታ ይፈጠራል።
ይህን ተከትሎም ውስጣዊና ውጫዊ ጫናን መቋቋም የሚሳነው መንግስት ለይቶለት ይፈርሳል። የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች መሳሪያቸውን እንደያዙ ይበተናሉ። በየብሔር ማንነታቸው እየተቧደኑ አማጺያንን ይቀላቀላሉ፣ አሊያም ሽፍታና ቀምቶ-አዳሪ ይሆናሉ። በጋራ አጀንዳ መተባባር የተሳናቸው አማጺያንም ማዕከሉን ለመቆጣጠር እርስ-በርስ መዋጋት ይጀምራሉ። አዲስ አበባና አካባቢዋ ዋና የጦርነት አውድማ ይሆናሉ።
የውጭ ኤምባሲዎች አገሪቱን ለቀው ይወጣሉ፣ አገሪቱም ከውጭው ዓለም ጋር ያላት ሁለንተናዊ ግንኙነት ይቋረጣል። የአየር በረራ ይቆማል፣ የስልክና የኢንተርኔት ግንኙነት ይቋረጣል፣ የድንበር ላይ ኬላዎች ይፈርሳሉ። ተራ ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት የያዙ የመንግሥት ባለስልጣናትም ሆኑ የተትረፈረፈ ገንዘብ ያላቸው ባለሃብቶች ከአገር መውጣት አይችሉም። የባንኮች መዋቅርም ስለሚፈርስ ከውስጥ ወደ ውጪ ገንዘብ ለማሸሽም ሆነ ከውጪ ወደ አገር ውስጥ ለተቸገረ ዘመድ ገንዘብ መላክ የማይቻል ይሆናል።”