የፓርቲ ፖለቲካ በኢትዮጵያ – ስሪትና እድገት: የመጽሐፍ ዳሰሳ

ግርማ ጉተማ (አባጫብሳ)፣ ከኦሮምያ

ሐምሌ 20 2017 ዓም

የመፅሐፉ ርእስ፥ የፓርቲ ፖለቲካ በኢትዮጵያ – ስሪትና እድገት

ጸሐፊ፥ ቤተልሔም ታፈሰ

የታተመበት አመት: 2017

የገጽ ብዛት: 304

አታሚ፥ ማንኩሳ ማተሚያ ቤት፣ ፊንፊኔ 

ሽፋን ገጽ ላይ የተጻፈው መሸጫ ዋጋ፥ ብር 600

ዳሰሳውን በ PDF ለማንበብ

1-መግቢያ

መጽሐፉ ያነሳው ርሰጉዳይ ጠለቅ ያለ አካዳሚያዊ ምርምር ጭምር የሚጠይቅ መሆኑ ግልጽ ነው። ከዚሁ አንጻር ይመስላል መጽሐፉን ሳነብ ያዩ ሁለት ወዳጆቼ፣ “ቤቲ መጽሐፉን ራሷ አልጻፈችውም፤ ሌሎች ጽፈው በስሟ አሳትመው ነው” የሚል አስተያየት ሰተውኛል። በዚህ አጭር የመጽሐፉ ዳሰሳዬ ውስጥ ግን ይሄ ጉዳይ የኔ ትኩረት አይሆንም። የዚህ ዓይነቱ መላምት ውስጥ መግባት አልሻም። ትኩረቴን ማድረግ የምፈልገው የመጽሐፉ ይዘት ላይ ብቻ ነው።

መጽሐፉ 3 ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ ባጠቃላይ 11 ምራፎችን በ304 ገጾች ውስጥ ቀብብቦ የያዘ ነው። በ10ኛው ምራፍ የ3 የቀድሞ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ቃለ መጠይቅ አካቷል። እነዚህም አቶ ፋሲካ ሲደልል ከኢሰፓ፣ አምባሳደር ታደለች ሃይለሚካኤል ከኢሃፓና ዶር ተስፋዬ ቤልጅጌ ከብልጽግና ናቸው።

በግርድፉ ሲታይ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የፓርቲ ፖለቲካ ጉዳይ በተመለከተ ከሚስተዋለው የሊህቃን ውይይት ድርቀት አንጻር፣ መጽሐፉ አንዳች ጠቃሚ ተዋጾ ማድረግ እንደሚችል መገመት ይቻላል። ከዚሁ አንጻር መጽሐፉ ውስጥ የተነሱትን አንዳንድ ነጥቦች አንስቶ ወደ ማየት ብንሄድ ጠቃሚ ይሆናል።

2-መጽሐፉ ያነሳቸው ጠቃሚ ጉዳዮች

መጽሐፉ በተለይም ኢህአዴግንና የቀድሞውን ቅንጅት በተመለከተ ያነሳቸው ነጥቦችና ያቀረባቸው “የውስጥ አዋቂ” የሚመስሉ ትንተናዎች ጠቃሚ ሆነው ይታያሉ። ኢህአዴግን በተመለከተ፣ ድርጅቱ እንዴት እንደፈረሰ ምናልባትም በአቶ ብርሃነ ጽጋብ (የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ አባል የነበረ) የኢህአዴግ የቁልቁለት ጉዞ (2005-2010) የስብሰባዎች ወግ በሚል ርእስ ከተጻፈው መጽሐፍ ለጥቆ፣ ጠለቅ ያሉ የውስጥ መረጃዎችን ማቅረብ የቻል ይመስላል ይሄ መጽሐፍ። በተጨማሪም፣ በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ሃገሪቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሸጋገር እንዳትችል ህወሓት/ኢህአዴግ ያመከናቸውን ታሪካዊ እድሎች በማነሳሳት ያቀረበው ትንተናዎች (ገጽ 172-193) የመጽሐፉን በጎ አበርክቶት የሚያሳይ ሆኖ ይታያል።

በዚሁ ረገድ “ቅንጅት” በሚል ስም ተመስርቶ ስለነበረውና በዶ/ር አለማየሁ አረዳ ቋንቋ “ባረጀ ሃሳብ የተዋቀረ አሮጌ መርከብ”፣ ወይም በአቶ በረከት ስምዖን ቋንቋ “እንዳሮጌ ብርድልብስ የተጣጣፈ ድርጅት” ስለተባለው የፖለቲካ ድርጅት በተመለከተ የቀረበው ትንተናም እውነታውን ያገናዘበ ሆኖ ይታያል። እንደተጠቀሰውም፣ በጥድፊያ በተሰባሰቡ አራት ባላንጣ ድርጅቶች የተፈጠረው ቅንጅት፣ ከህወሓት ኢሃድግም ባልተናነሰ መጠን በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ላይ አሉታዊ አስተዋጾ አድርጓል። ያ ድርጅት በዚህ ረገድ የፈጸማቸውና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ወደኋላ መንሸራተት ከፍተኛ አስተዋጾ ያበረከቱ ድርጊቶች በዚህ መጽሐፍ ገጽ 222-224 ተብራርተዋል። በነገራችን ላይ፣ ቅንጅቱን ካቋቋሙት አራት ድርጅቶች ያንዱ መስራችና መሪ የነበረው ዶ/ር አለማየሁ አረዳ በቅርቡ በሰጠው አንድ ቃለመጠይቅ፣ “ቅንጅት ባረጀ ሃሳብ የተዋቀረ አሮጌ መርከብ ነበር፣ እዛ ውስጥ የገባነው በህዝብ ግፊት ሲሆን አሮጌው መርከብ ተፈረካክሶ መስመጥ ሲጀምር ዘለን እንወርዳለን በሚል የፖለቲካ ካልኩሌሽን ነበር“ ሲል ሰምተነዋል። የሰውየው አባባል ስለድርጅቱ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የቀረቡትን ትንተናዎች የሚያጠናክር ነው።

በተጨማሪም ድርጅቱ በዛ ምርጫ ላይ ይዞት የመጣው የፖለቲካ ትርክትና ስልት፣ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምህዳር በብዙ መልኩ የመረዘና ያበላሸ ስለመሆኑ በግልጽ አስቀምጦታል መጽሐፉ። አካሄዱ በኢትዮጵያ የግራና የቀኝ ፖለቲካ ሃይሎችን ልዩነት ያሰፋም ብቻ ሳይሆን፣ ባገሪቱ የፖለቲካ ሊህቃን ዘንድም አለመተማመን እንዲሰርጽ ያደረገ ነው ማለት ይቻላል። የዚህ መጽሐፍ ትንተና ከዚህ በላይ ገፍቶ ባይሄድበትም ቅሉ፣ ያ የተጣጠፈና አሁን የሞተው ቅንጅት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ላይ ጥሎት ያለፈው አሉታዎ ተጽኖ እስከዚኛው የብልጽግና አገዛዝ ዘመን ጭምር የዘለቀ ነው ማለት ይቻላል። ይኻውም በውስጣዊ አንድነት ሳይሆን በህዝብ ግፊት ብቻ አንድ ላይ ተጣምሮ የነበረው ድርጅት ሲፈርስና፣ ፓርላማ አንገባም ያሉት መሪዎቹ ታስረው ከተለቀቁ በኋላ ወደ ውጭ ሃገር ተሰደው የድርጅቱን ሙት መንፈስ ለማስቀጠል ሞከሩ። በዚሁም “ኢሳት” የተባለ በኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ በግልጽ የዘር ማጥፋት ትርክት (genocidal narrative) ጭምር የሚያውጅ ሚዲያ አቋቋሙ። በዚሁ ሚዲያ ዙሪያ ተኮልኩለው በተለይም በኦሮምያና በትግራይ ላይ ሲያካሂዱት የነበረው ጸረ-ህዝብ ፕሮፓጋንዳቸው የሚዘነጋ አይደለም።

ኋላ በ2018 ለውጥ መጣ ሲባልም፣ ከማንም ቀድመው ግር ብለው ገብተው አሁን ላለው አገዛዝ ፍጹማዊ ድጋፍ (blanck cheque support) ሊባል የሚችል ዓይነት ድጋፍ ሰጡ። ኢትዮጵያን ሊያፈስ የመጣ ሃይል በሌለበት ሁናቴ፣ “ሃገር ማዳን” የሚል ረብ-የለሽ ፕሮፓጋንዳ ለስርዓቱ አገዛዝ መሪዎች በማቀበል፣ ሃገሪቱን ወደ አስከፊ የስርበርስ ጦርነት በመግፋት ረገድ የዚሁ ድርጅት መንፈስ ወራሾች ግንባር ቀደም መሆናቸው ሊካድ አይችልም። ወደ ጦርነት ከተገባ በኋላም ጦርነቶችን ደግፎ በማፋፋምና ባገዛዙ ላይ በጥገኝነት ተለጥፈው እስከ ዛሬዋ ቀን የዘለቀ ነው ማለት ይቻላል ሚናቸው። የመንፈሱ ወራሾች፣ ቀጣይ የርስ በርስ ጦርነቶችንም በተመሳሳይ መልኩ እንደሚደግፉ የሚናገሩት በግልጽ ቋንቋ ነው። ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት፣ መጽሐፉ እዚ ድረስ ገፍቶ ባይሄድም፣ የዛን ድርጅት የፖለቲካ አሉታዊ ሌጋሲ ከኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ትግል አንጻር ለማየት መሞከሩ የመጽሐፉ አንዱ በጎ አስተዋጾ ነው።

3 በመጽሐፉ ወስጥ የሚታዩ ውስንነቶች

በኔ እይታ መጽሐፉ በርከት ያሉ ውስንነቶችም ያለበት ነው። ከአርስቱ የሚጀምር የአርትዖት ችግር ሰለባ መሆኑ ግን ትንሽ ግር የሚል ነገር አለው። የሽፋን ገጹ ርእስ “የፓርቲ ፓለቲካ…” ይላል። ትኩረት ከመሳብ ይሆን እንዴ ሆን ተብሎ የሆሄያት ግድፈት የተደረገው፧ ብዬ አንድ አማርኛ መምህር የሆነ ወዳጄን ባማክረው፣ “ እንዲያ ተደርጎ ከሆነ እብደት ነው” ብሎኛል። በመጽሐፉ የውስጥ ገጾች ውስጥም በርከት ያሉ የአርትዖት ግድፈቶችን ማየት ይቻላል።

ከርእሱ ጋር በተያያዘ ሌላም ሊነሳ የሚችል ጉዳይ አለ። ርእሱ Generic Title (ተደጋግሞ ሊጻፍበት የሚችል ዓይነት) ሊሆን የመቻሉን ያህል፣ ጸሐፊዋ በዚህ ርእሰ ጉዳይ መጽሐፍ ለመጻፍ ስትነሳ፣ ቢያንስ ከዚህ ቀደም በዚሁ ርእስ ወይም በተቀራራቢ የተጻፉ ሊትሬቸሮችን ማንበብ ብቻም ሳይሆን፣ በተገቢው ቦታ ማጣቀስም ተገቢ ነበር። ለምሳሌ የኦፌኮ ከፍተኛ አመራር (ዋና ጸሐፊ) የሆኑት ኦቦ ጥሩነህ ገምታ ቀደም ብሎ በዚሁ ርእስ መጽሐፍ ጽፈው ያሳተሙ ሲሆን፣ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ አንድም ቦታ አልተጣቀሰም (cite አልተደረገም)። ይህ ማለት ይሄ መጽሐፍ ሲጻፍ በጉዳዩ ላይ ተጽፈው ባደሩ ሎትሬቸሮች ላይ በቂ ዳሰሳ አልተደረገም ማለት ይሆናል። በውጤቱም ሌሎች ቀድሞ የጻተፉትን ጉዳይ በመድገም አንባቢያንን ማሰልቸት ብቻም ሳይሆን ጊዜና ሃብት ማባከንንም የሚያስከትል ይሆናል።

የመጽሐፉ ዓላማ በተገለጸበት የመግቢያው ክፍል፣ “…ሃገር የማስተዳደር እድል ያገኙና ያላገኙ ፓርቲዎች ያለፉበትን መንገድ በመፈተሽ የፖለቲካ ባህላችን ስሪትና እድገት የገጠመውን ስብራት ቃኝቶ መድሃኒቱን ይጠቁማል። በዚህም፣ ዛሬ ላይ መሰረቱን በማቅናት፣ መጪው ትውልድ ስልጡን ፖለቲካና በስልጡን የፓርቲ አደረጃጀት መራመድ እንዲችል መንገድ ማሳያ ሰነድ ነው።” ይለናል። እዚጋ ሰነዱ የነማን ሰነድ ነው? ቃላት አጣጣሉስ የነማንን ይሸታል? የሚለውን ወሳኝ ጥያቄ ለጠያቂዎችና ለአሽታቾች እንተውና፣ መጽሐፉ በጣም የተለጠጠ ዓላም (over ambitious aim) ይዞ የተነሳ ሆኖ ይታያል። ከንባቤ ተነስቼ ሳየውም፣ “መድሃኒት የመጠቆም” ዓላማውን ማሳካት የቻለ አይመስለኝም።

ሌላው የመጽሐፉ ስብራት ሊባል የሚችለው ጉዳይ (ያው እኔም የብልጽግናን ቋንቋ ብጠቀም ችግር የለውም ብዬ ነው)፣ ያነሳውን ርእሰጉዳይ ሲያብላላ በዋናነት ትኩረት የሚያደርገው የዛሬይቱን ኢትዮጵያ ማህበረ-ፖለቲካዊ ሁናቴዎችን በመበየን (define በማድረግ) ረገድ ብዙም ተጨባጭ ሚና ባልነበራቸው እንደ ኢህአፓና መኢሶን በመሳሰሉ ፓርቲዎች ላይ በጣም በሰፊው የሚያጠነጥን መሆኑ ነው።

ከዚህ አንጻር ሲታይ፣ መጽሐፉ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ዲስኮርስ ውስጥ በግልጽ የሚታየውና ባማርኛ ስነጽሁፍ ውስጥ በጣም ተዛብቶ የቀጠለው ትርክት ሰለባ መሆኑ በግልጽ ይታያል። ይሄ ማለት ምን ማለት ነው? የዛሬይቷን ፌዴራላዊት ኢትዮጵያን በማዋቀር ረገድ ኢህአፓ፣ መኢሶን ወይም ደርግ/ኢሰፓ አስተዋጾአቸው ምንም ነው ማለት ይቻላል። ነገር ግን ባለፉት ሶስት አስርታት ባማርኛ ቋንቋ ስለሃገሪቱ የተጻፉትን ሊትሬቸሮች ብዛት ብናይ፣ ከነዚህ ሶስቱ የፖለቲካ ቡድኖች የወጡ ሊህቃን የጻፏቸው መጽሐፍት ብዛት በኔ ግምት ምናልባትም ከመቶ በላይ ይሆናሉ። በተቃራኒው ግን ህብረ-ብሄራዊውን ፌዴራሊዝም ጨምሮ የሃገሪቱን ወሳኝና ነባራዊ ፖለቲካዊ መዋቅሮችንና ኹነቶችን ከበየኑት የፖለቲካ ሃይሎች፣ ማለትም ኢህአዴግ ውስጥ ከነበሩት አራት ፓርቲዎችና ከኦነግ ጨምሮ የወጡ ሊህቃን ባሉፉት ሰላሳ ዓመታት የጻፏቸው የመጽሐፍ ብዛት ከነዛዎቹ አንጻር (አሁንም በኔ ግምት) ሩብ እንኳን የሚሆኑ አይመስለኝም። ይሄ ማለት ባማርኛ ቋንቋ የተጻፉትን ሊትሬቸሮች ብዛት እንደ ፓርቲዎቹ ተጽኖ ፈጣሪነት ከወሰዳቹ በትልቁ ትሸወዳላቹ። ምንክንያቱም ከዛ አንጻር ካያቹት በገብያ ውስጥ ገዥ ትርክት መስሎ የሚታየው (false positive impression) የነ ኢህአፓ-ወ-ኢሰፓ ትርክት ነው። ይሄ መሆን የቻለው ደግሞ ሃሳባቸው የመንግስት ስልጣንን የተቀጣጠረው የጠቀስኳቸው የፖለቲካ ሃይሎች ብዙ ስላልጻፉ ነው። የመጽሐፉ 65% የሚሆኑ ገጾች በኢህአፓ-ወ-ኢሰፓ ጉዳዮች ላይ መዋላቸው፣ መጽሐፉ የዚህ የተዛባ ትርክት ሰለባ ስለመሆኑ ያቀረብኩትን መከራከሪያ ነጥብ የሚያስረግጥ ነው።

መጽሐፉ በህወሓት ጉዳዮች ላይ (ብቻውንም ከኢህአዴግ ጋርም ጨምሮ) አምስት ደርዘን የሚሆኑ ገጾችን ያጠፋ ሲሆን፣ ኦነግም በግርጌ ማስታወሽ ደረጃ ባለ የገጾች ብዛት ተዳሷል። ሌሎች እንደ ኦፌኮ ያሉና ህዝባዊ መሰረት ያላቸው ፓርቲዎች ግን በመጽሐፉ ውስጥ አንድም ቦታ እንኳን አልተጠቀሱም። የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር መረራ ስሙ ሶስት ጊዜ ተጠቅሷል፥ አንዴ በ2007 Party politics, political polarization and the future of Ethiopian democracy በሚል ርእስ ከታተመው አካዳሚያዊ ስራው ጋር ተያይዞ፣ ሁለቴ ደግሞ እግረመንገድ…አቶ ፋሲካ ሲደልል አንዴ በቃለመጠይቁ ውስጥ ካነሳው ጨምሮ ማለት ነው። በርግጥ ኦፌኮ ብቻም ሳይሆን ሌሎች ነባርና በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ትግል ውስጥ አስተዋጾ እያደረጉ የቆዩና ያሉ ፓርቲዎች መኖራቸውም የሚታወቅ ነው። በዚ መጽሐፍ ውስጥ አንዳቸውም ግን አልተጠቀሱም።

መቼም እንደ ኦፌኮ ከዴሞክራሲ አንጻር ምርጫ ገርበብ ተደርጎም ቢሆን ሲከፈት ለጨፌ ኦሮምያ 115 እጩዎችን፣ ለፌዴራሉ ፓርላማ ደግሞ 53 እጩዎቹን በማስመረጥ ጭምር ባለፉት ሁለት አስርታት በላይ ለዴሞክራሲያዊ ትግሉ አስተዋጾ እያደረገ ያለን ፓርቲ በዚህ ርእስ መጽሐፍ ሲጻፍ አንስቶ አለመገምገም፣ መጽሐፉን ጎደሎ (incomplete) የሚያደርገው መሆኑ አያጠራጥርም።

መጽሐፉ አንዳንድ የተዛቡ መረጃዎችንም የያዘ ነው…የሃሰት መረጃዎች ላለማለት። ሁለት ነጥቦችን ብቻ በምሳሌነት እናንሳ፥ 1) ለሰለሞናዊው ስርወ መንግስት መሰረት የሆነውን የቀዳማዊ ምንሊክ ንግርት (legend)፣ እንደ የታሪክ እውነታ (historical fact) አስመስሎ ያቀርባል መጽሐፉ (ገጽ 12 )። 2) መጽሐፉ ስለኦነግ ጥቂት መረጃዎችን ባቀረበበት ክፍል፣ የሶማሊያው ዚያድ ባሬ ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ፣ ድርጅቱ ከሶማሊያ መንግስት የጦር መሳሪያ አግኝቶ ስለመጠናከሩ በገጽ 104 ላይ ገልጿል። አንድም ምንጭ ግን አልጠቀሰም። በኔ አረዳድ እነዚ የሃሰት መረጃዎች ናቸው። አሁንም ድረስ በህይወት ያሉ የቀድሞ የድርጅቱ መሪዎች በየቃለመጠይቆቻቸው ሲሉ የሰማነው ተቃራኒውን ነው። ዚያድ ባሬ ኢትዮጵያን የወረረው የኦሮምያን ግማሹን መሬት (ከአዋሽ በታች ያለውን ሃገር ሁላ) ወደ ታላቋ ሶማሊያ ለማጠቃለል ዓላማ ይዞ የመሆኑ የታሪክ እውነታ እየታወቀ፣ “በወረራው ጊዜ ኦነግ የዚያድ ባሬን ወረራ ደግፎ፣ ከሶማሊያ መንግስት የጦር መሳሪያ አገኜ” የሚለው ነገር ትርጉም አይሰጥም። የሚታወቀው ታሪክ በወቅቱ የነበረው የኦነግ ጦር ኦጋዴን ውስጥ ጭምር ገብቶ የወራሪውን የዚያድባሬ ጦር ስለመዋጋቱ ነው።

ከዚህ ዓይነቱ ተዛብተው ከሚጻፉ መረጃዎች ጋር በተያያዘ ግን አንድ ነገር ሁሌም ይገርመኛል። ኦነግ እንደ ድርጅት የሌለ ያህል፣ የዚህ ዓይነቱ የፈጠራ መረጃዎች በየመጽሐፍቱ ታትመው ሲሰራጩበት ራሱን ለመከላከል ምንም አይሞክርም። የድርጅቱ አባል ያልሆንኩት እኔ ራሴ እንኳን፣ በዚህ መጽሐፍ ጨምሮ ቢያንስ ባምስት መጽሐፍት ውስጥ ይሄን ዓይነቱን ነገር በመታዘብ እውነታውን ለመከላከል መሞከሬን አስታውሳለው። ሌላው ሳይጠቀስ ማለፍ የማይገባው ጉዳይ፣ በመጽሐፉ ውስጥ በሰፊው የሚታየው የሃሳቦች መደጋገም ነው። በኔ soft critique፣ በሰፊው የሚታየውን የሃሳቦች መደጋገም ማስቀረት ቢቻል የዚህን መጽሐፍ ገጾች ብዛት በግማሽ ያህል መቀነስ ይቻል ነበር ባይ ነኝ።

በመጨረሻም፣ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በመጽሐፉ የማጠቃለያ ክፍል ላይ፣ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ እሳቤ” በሚል ባነሳው ጉዳይ ላይ የውይይት ሃሳብ ወይም ጥያቄ ወርውሬ ላብቃ። “ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ“ የሚለውን ጉዳይ አሁን ባለው መንግስት ውስጥ በከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ ያሉ ግለሰቦች ሲያነሱት ተስፋዬ በልጅጌ የመጀመሪያው አይደለም። ዲያቆን ዳንኤል ክብረትም “የትርክት እዳና በረከት” በሚል ርእስ በቅርቡ ባሳተመው መጽሐፍ ገጽ 554 ላይ አንስቶታል። ዲያቆኑ የዚህን ፖለቲካዊ ተርም ትርጓሜ አላብራራም። ዶ/ር ቤልጅጌ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በተካተተው ቃለ መጠይቁ ግን እሳቤውን ከኦሮሞ ገዳ ስርዓት ጋር በቀጥታ አገናኝቶታል። የኦሮሞ ገዳ ለዛሬዋ ፌዴራላዊት ኢትዮጵያ እንዴት ተመራጭ ስርዓት ሊሆን እንደሚችል ግን በዝርዝር አልሄደበትም።

የሆነው ሆኖ… አንድ አቶ ፋሲካ ሲደልልም እዚሁ መጽሐፍ ውስጥ የጠቀሰውን ወሳኝ ነጥብ እዚ ላይ መልሶ ማንሳት ተገቢ ይሆናል። ዴሞክራሲንና ሳይንስና ቴክኖሎጂን የመሳሰሉ Universalist እሳቤዎችን ያቀፉ ጉዳዮች፣ የግድ “ኢትዮጵያዊ” ለማድረግ የሌለ ሃቲት ለመፍጠር መሞከር ተገቢ አይሆንም። አሁን ያለው አገዛዝ የዚህ ዓይነቱን ሃሳዊ መንገድ ተከትሎ “ሃገር-በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም/Home Grown Economic Reform“ ብሎ ሲያበቃ፣ የነ IMFን ጸረ-ህዝብ ጸረ-ድሃ ፖሊሲ ስራ ላይ ለማዋል ሲፈጨረጨር የማየታችን ምክንያቱ ይሄው ነው።

አበቃሁ።

Editor’s Disclaimer:
The views and opinions expressed in articles published by UMD Media are those of the authors and do not necessarily reflect the official position or editorial stance of UMD Media. Publication does not imply endorsement.

Call for Contributions:
UMD Media welcomes contributions from readers, including opinion pieces, articles, rejoinders, and critical analyses in Tigrigna, Amharic or English. We encourage diverse perspectives and thoughtful engagement on the issues that matter. Submissions can be sent to our editorial team for review. While we may not publish every submission, we are committed to fostering open dialogue and informed public discourse.

Subscribe to our multilingual YouTube channel at youtube.com/UMDMedia 

Scroll to Top