ግርማ ጉተማ (አባጨብሳ) ከኦሮምያ
August 7, 2024
የመጽሐፉ ርዕስ፥ የትርክት እዳና በረከት
አታሚ፥ ኢክሊፕስ ማተሚያ ቤት (የመጀመሪያ እትም 2016)
የሽፋን ገጽ ላይ የተቀመጠው መሸጫ ዋጋ፥ ብር 1000
1) መግቢያ
መጽሐፉ በ6 ክፍሎች 46 ምዕራፊችን ይዞ በ575 ገጾች ተቀብብቦ የቀረበ ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም የኢትዮጵያ ሃገረ መንግስት በዘላቂነት የሚቆምበትን “ታላቁን ትርክት” መፍጠር ወይም ማበጀት ስለመሆኑ ተገልጿል።
ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በህይወት እያለ፣ ዳንኤል ክብረት ኢትዮጵያ ውስጥ የመሃል ፖለቲካ ሻምፒዮን (champion of centrist politics) ሆኖ ሊመጣ ይችላል ብሎ ያሰበ አለ? እዚህ መጽሐፍ ውስጥ ለመፍጠር የተሞከረው ይሄ ነው። ይሄን ሲያደርግ ፕሮፌሰር መረራን አንድ ቦታ ላይ በበጎ አንስቶት ንግግሩንም ይጠቅሰዋል (ገጽ 124—135)።
በሌላ የመጽሐፉ ክፍል ግን (ገጽ 46–65) የፕሮፌሰር መረራን የቆየና በሰፊው የሚታወቅ ሳይንሳዊ እሳቤ በገፍ ዘርፎ ሲያበቃ፣ ጥቂት ዝርዝር ጉዳዮችን ብቻ በማከል ልክ እንደራሱ ኦሪጂናሌ ሃሳብ አድርጎ አቅርቧል። የOppression thesis፣ colonial thesis፣ re-unification thesis የመሳሰሉትን (ሲጠቃለሉ Merera’s Thesis) የሚባሉትን ልክ እንደራሱ ሳይንሳዊ ሃሳብ አድርጎ አቅርቧል። በዚህ መጽሐፉ የፕሮፌሰር መረራን ሳይንሳዊ ጥናቶች ሳይጠቅስ ይሄን ማድረጉ ትልቅ ትዝብት ውስጥ የሚጥለው መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።
አንዳንድ ወዳጆቼ “አባጫብሳ አንተ ሞኝ ነህ እንዴ የዳንኤል ክብረትን መጽሐፍ በ1300 ብር ገዝተህ የምታነበው…ገንዘብና ጊዜ ተረፈህ እንዴ?” በማለት maal baasuuf dharma raasuu የሚለውን የኦሮሞ wisdom አባባል ወይም ተረት ተርተውብኛል።
ሆኖም ግን እኔ አሁንም ቢሆን መጽሐፉን ለማንበብ በቂ ምክንያቶች ነበሩኝ ባይ ነኝ።
ጥቂት ላብራራ…
መጽሐፉ ሲመረቅ ጠቅላይ ምንስትሩንና ምክትል ጠቅላይ ምንስትሩን ጨምሮ ብዙዎቹ የፌዴራልና የክልል መንግስታት ካቢኔ አባላት ተገኝተው እንደነበር ይታወሳል። ይሄ ኹነት መጽሐፉ የአንድ የሚታወቅ ዲያቆን መጽሐፍ ሳይሆን፣ የዚህ መንግስት የፖለቲካ ማኒፌስቶ ስለመሆኑ በግልጽ ያመላከተ ነው። እንደፖለቲካ ሰው ደግሞ ይሄ ዓይነቱ ወሳኝ ክስተት (major event) ትኩረቴን ካልሳበው ምን ዓይነት ነገር ሊስበው ይችላል?
2) የመጽሐፉ ጠንካራ ጎኖች
መጽሐፉ በተለይም የጊዜውን የኢትዮጵያ ፖለቲካን የሚከታተሉ ሰዎችና በቀጥታ ፖለቲካ ውስጥ የሚሳተፉትን ትኩረት ሊስቡ የሚችሉ ጉዳዮችን የሚያነሳሳ በመሆኑ፣ ንባብን የሚጋብዝ ሆኖ ይታያል። ከዚህ አንጻር ያነሳሳቸውን አንዳንድ ነጥቦችን ብንመለከት፥
—መጽሐፉ የብልጽግናው አገዛዝ የሚያልማት ኢትዮጵያ ምን እንደምትመስል ብቻም ሳይሆን፣ ያቺን ኢትዮጵያ ለመፍጠር የሚሄዱበትን መንገድ ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ሞክሯል። “መደመር” የተባለው ያገዛዙ ማኑዋልም፣ ፍልስፍናም የፖሊቲካ ርዮተ ዓለምም እንደሆነ በግልጽ ቋንቋ ነግሮናል።
—ጸሐፊው ዳንኤል ክብረት (በሌሎች መጽሐፍቱ ላይ ይጠቀምበት የነበረውን ሃይማኖታዊ መዕረግ “ዲያቆን” እዚኛው ላይ ማስወገዱ ትኩረቴን ሳይስበው አልቀረም) ቀደም ብሎ የሚታወቅባቸውን ያፈጠጡ ጸረ እስልምናና ጸረ ኦሮሞ አቋሞቹን በዚህኛው መጽሐፉ ውስጥ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ያለዘበ ሆኖ ይታያል። ለምሳሌ በፊት በዘፈቀደ ይጠቀምባቸው የነበሩትን “የእስላሞች ወረራ”፣ “የአህመድ ግራኝ ወረራ”፣ “የኦሮሞ ወረራ”… የመሳሰሉትን ዓይነት አሉታዊ አገላለጾች (negative expressions) ከመጠቀም ተቆጥቦ ሲያበቃ፣ በምትካቸው “የእስላሞችና የክርቲያኖች ግጭት/ጦርነት”፣ እንዲሁም “የኦሮሞ ህዝብ መስፋፋት” እያለ ለመጻፍ ሞክሯል። ጸሐፊው ከወጣበት ወግ አጥባቂ ኦርቶዶክሳዊ (conservative and orthodoxy) መሰረቱ አንጻር ሲታይና ከዚህ ቀደም ይጽፋቸውና ይናገራቸው ከነበሩት ነገሮች አንጻር፣ በዚህ ረገድ የታሪክ እይታውን ለማሻሻል ወይም ለማለዘብ ብርቱ ጥረት እንዳደረገ ማጤን ይቻላል።
—በተጨማሪም፣ ምንም እንኳን አንዳንድ ጉዳዮችን አለባብሶ ሲያልፍ ቢስተዋልም (ለምሳሌ “የምስራቅ አማራ ፋኖ” የሚባለውን ቡድን ያደራጁት በፌዴራልና በክልል ደረጃ ከፍተኛ ስልጣን የነበራቸው አኩራፊዎች እንደነበሩ አስቀምጦ ሲያበቃ፣ እነዚህ ሰዎች እነማን እንደሆኑ ግን ደብቆ ያልፋል)፣ ስለ አማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ያቀረበው ግምገማ ትክክል ከሆነ፣ ለብዙዎቻችን አዳዲስ የሆኑ መረጃዎችን የያዘ ነው። መረጃዎቹ የፖለቲካ ብቻም ሳይሆን የታሪክና ወታደራዊ አንድምታዎችም ያላቸው በመሆኑ ጠቃሚ ናቸው።
3) የመጽሐፉ አንዳንድ ውስንነቶች
መጽሐፉ በቆዩ የታሪክ ኹነቶች ላይ ብቻም ሳይሆን፣ ብዙዎቻችን በምናውቃቸው የቅርብ ጊዜ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ክስተቶች ላይ ወይ ሃሰተኛ የሆኑ ጥሬ መረጃዎችን ወይም ደግም የተዛቡ ትንተናዎችን በብዛት የያዘ ነው። የመጽሐፉ ዋነኛ ችግርም ይሄ ነውና እዚሁ ላይ ትኩረት በማድረግ አንዳንድ ነጥቦችን በማሳያነት ላንሳ፥
—ደርግና ኢህአዴግ በብሄረሰቦች ጭቆና ጉዳይ ላይ አንድ ዓይነት አተያይ ያለቸው ስለመሆኑ (ገጽ 61)…ይሄን በተመለከተ ፍርዱን ላንባቢ ልተው፤
—ኦነግና ህወሓት “ጨቋኛና ተጨቋኝ ብሄር አለ” የሚል አቋም የሚያራምዱ ስለመሆናቸው (ገጽ 63)… እነዚ የፖለቲካ ድርጅቶች አሁንም አሉ አቋማቸውንም ማስረዳት የሚችሉ ናቸው፣ ነገር ግን የዚህ ዓይነት አቋም እንደማያራምዱ ሲገልጹ በተደጋጋሚ ሰምተናቸው እናውቃለን፤
—ደርግ የፖለቲካ ድርጅት ስለመሆኑ (ገጽ 63)…ደርግ ጊዜአዊ የታደሮች ኮሚቴ እንጂ የፖለቲካ ድርጅት እንዳልነበር በታሪክ ይታወቃል፤
—የኢትዮጵያ ሃገረ መንግስት ሶማሊኛ፣ ከፍኛ፣ ሃድይኛ፣ ዓረብኛ፣ ኦሮምኛ፣ ሃረሪኛ… የመሳሰሉትን ቋንቋዎች ይጠቀም እንደነበር (ገጽ 83)… ኢትዮጵያ ማለት ዛሬ የምናውቃት ኢትዮጵያ ከሆነች ይሄ ነጭ ውሸት ነው፤
—በሃይለስላሴ የመጨረሻው ዓመት ተረቀቀ የሚባለውንና ፈጽሞ ስራ ላይም ያልዋለውን ህገ መንግስት በማጣቀስ በንጉሱ ዘመን የብሄረሰቦች ቋንቋ ድፍጠጣ እንዳልነበረ የሚገልጽበት (ገጽ 84)… አሁን ይሄ ምን እንበለው? ነጭ ውሸት ወይስ የተዛባ ትንተና?
—ከ1923 በፊት የኢትዮጵያ መንግስት በይፋ የሚቀበለው አንድም የስራና ብሄራዊ ቋንቋ እንዳልነበረው (ገጽ 83)… እነ እምዬ ምኒሊክ በወፍ ቋንቋ ነበር’ንዴ የመንግስታቸውን ስራዎች የሚያከናውኑት?
—ህወሃቶች እንደ አጼ ዮሃንስ ያሉትን የራሳቸው ወገን የሆኑ የፊውዳል መሳፍንቶችን እንደሚደግፉና፣ እንደ ምንሊክ ያሉትን የአማራ ፊውዳል አጼዎችን ግን ለይተው በታሪክ ውስጥ እንደሚወነጅሉ (ገጽ 168)… ህወሓትንም ኦነግንም ጨምሮ ከኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ የሚቀዱ የግራ ዘመም ፖለቲካ ሃይሎች ጸረ ኢምፔሪያሊዝም አቋም እንዳላቸውና የየራሳቸውንም አካባባዊ ፊውዳል መሳፍንቶች በጠላትነት ጭምር ፈርጀው እንደሚታገሉ የሚታወቅ እውነታ ነው፤ ኦነግ እነጎበናን ህወሓት የትግራይ ፊውዳል መሳፍንቶችን “ጸረ ህዝብ” አድርገው እንደሚፈርጁ አይታወቅም’ንዴ ጎበዝ?
—ኢዴመአን ይባል የነበረውና እነሱሌይማን ደደፎና ተስፋዬ ገብረዓብ የመሳሰሉት ዛሬ በስም የሚታወቁ የደርግ ሙርኮኛ መኮንኖች ድርጅት ከኦህዴድ በፊት የተቋቋመና የኢህአዴግ መስራች አባል ድርጅት ስለመሆኑ (ገጽ 188)…ይሄ ድርጅት እነመለስ የፈጠሩት መሆኑ ሃቅ ቢሆንም የኢህአዴግ አባል ድርጅት እንዳልነበረ ግን ይታወቃል። የሽግግር ምክር ቤት ውስጥም ከኢህአዴግ ውጭ አንድ ይሆን ሁለት ወንበር የነበረው ሲሆን፣ የተፈጠረውም ጸሐፊው እዚ መጽሐፍ ውስጥ እንደሚለው ከኦህዴድ በኋላ እንጂ በፊት እንዳልነበር የሚታወቅ ነው። እርግጥ ኋላ ላይ ያ ድርጅት ሲበተን፣ አባላቱ ወደ አራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ገብተዋል። ለምሳሌ ሱለይማን ደደፎ ወደ ኦህዴድ፣ ተስፋዬ ገብረዓብ ወደ ህወሓት (በትግርኛ ተናጋሪነት) የተቀላቀሉት በዚህ መልኩ እንደነበር እናውቃለን፤ በጉዳዩ ላይም ቀደም ብሎ ብዙ የተጻፈበት ነው።
—በሽግግር መንግስቱ ውስጥ ኢህአዴግ 31 በመቶ ኦነግ ደግሞ 12 በመቶ መቀመጫ የነበራቸው ስለመሆኑ (ገጽ 189)…እውነታው ግን አራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እያንዳንዳቸው 12 ወንበሮች (ማለትም ኢህአዴግ ባጠቃላይ 4X12=48 ወንበሮች)፣ ኦነግም 12 ወንበሮች ነው የነበሯቸው። በመቶኛ ቢሰላም ዲያቂኑ እዚ ላይ የሚለው ነጭ ውሸት ነው፤
—የሃጫሉን ግድያ ተከትሎ የታሰሩት የኦሮሞ የፖለቲካ ሃይሎች የታሰሩበት ምክንያት መንግስትን ለመገልበጥ ስለተንቀሳቀሱ እንደሆነ (ገጽ 235)… ይሄንንስ ምን እንበለው? ቅጥፈት የሚለው ቃል አያንሰውም?
—የኢትዮጵያ መንግስታት ሁሌም የውስጥ አማጽያንን ድል ሲያደርጉ እንደነበርና በውስጥ አማጺያን ተሸንፈው እንደማያውቁ (ገጽ 253)… እውነታው ግን ተቃራኒው መሆኑ የሚታወቅ ነው፤
—ደርግ የውስጥ አማጺያንን ድል አድርጎ እንደነበርና የተሸነፈው ግን ለሰላም ስምምነት ባለመጽናት ስለመሆኑ (ገጽ 254)… ይሄ የታሪክ ፈጠራ ፈገግ አያሰኝም ወይ?
—ቤተ አምሃራ የሚባለ ፓርቲ በወያኔዎች ተመስርቶ እንደነበር (ገጽ 263)… “አረ በለው” አለ አማራ…፤
—‘ንጹህ ውሃ ያደፈረሰው የኦነጉ ሊቅ’…ነገሮች ቀጥተኛ ቅርጽ ይዘው በነበረበት ወቅት ድብልቁ/ድፍርሱ የተማሪዎች ንቅናቄ መጥቶ እንዳደፈረሰው (ገጽ 348)…የተማሪውን ንቅናቄ ጨምሮ የኢትዮጵያ ተራማጆችን ትግል ባሉታዊነት ፈርጆ ሲያበቃ፣ ነገሮች “ቀጥተኛ ቅርጽ” ይዘው ወደ ነበሩበት የድሮው ስርዓት እንመለስ ባይ ነው፤
—ኦነግ ያጤዎቹ ስርዓት ጥቂት ሊህቃን ያጠፏቸውን ጥፋቶች ላማራ ህዝብ ጠቅልሎ በመስጠት ህዝብን በጠላትነት እንደፈረጀ (ገጽ 360)…ዳንኤል እንዲህ በድፍረት ሲቀጥፍና ሲወነጅል ኦነግ ራሱን መከላከል አይችልም ብሎ የደመደመ ይመስላል። ኦነግ ያማራን ህዝብ እንደህዝብ በጠላትነት የፈረጀው የትና መቼ ይሆን ግን? ኦነግ በርግጥም በህይወት ካለ፣ ወጥቶ ራሱን መከላከል ያለበት ይመስለኛል።
- በክፍል አምስት “ቀደምት የኢትዮጵያ አንዳንድ የስልጣኔ መልኮች” በሚለው የመጽሐፉ ክፍል (ገጽ 372 — 513)፣ ዳንኤል በተለይም በደርግና ባጤው ዘመን የመደበኛ ትምህርት ካሪኩለም ውስጥ ጭምር ነበሩ የሚባሉትን የተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ነጠላ የታሪክ ትርክት (regional historiographies) እየመራረጠ ለማቅረብ ብዙ ለፍቷል። ይሄን ሲያደርግ ደግሞ ራሱ ቀደም ብሎ የጻፋቸውን ተረታ ተረት የበዛባቸውን መጽሐፍቶቹን በምንጭነት በሰፊው ተጠቅሟል። እዚህ መጽሐፍ ላይም ያው ልክ እንደጥንቱ “የኢትዮጵያ ታሪክ”፣ ኦሮሞ በጥፋትም ሆነ በስልጣኔ ሲጠቀስ፣ በጎሳ ተበታትኖና ተከፋፍሎ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
4) ታላቁ ትርክት ወይስ ታላቁ ተቃርኖ?
ጸሐፊው ዳንኤል በግልጽ እንዳስቀመጠው፣ የመጽሐፉ ዋና ዓላማ እሱና እሱ በካቢኔ አባልነት ያለበት የብልጽግና አገዛዝ imagine ለሚያደርጓት ኢትዮጵያ “ታላቁን ትርክት” መፍጠር ነው። ጸሐፊው በግልጽ ሊነግረን እንደሚሞክረው ደግሞ፣ ይሄ ዓይነቱ ትርክት የሚዋቀረው ሃገረ መንግስቱን በተመለከተ ቀደም ብሎ ከነበሩት ሁለት ተጻራሪ ትርክቶች አንጻር አማካዩን ስፍራ (the middle ground) በመያዝ ነው።
ይሄውም ማለት ሊፈጠር የተፈለገው “ታላቁ ትርክት” እንደ ያጤዎቹ ወይም የነፍጠኞቹ ዘመን የብሄሮችን መብቶች ጨፍላቂ “የኢትዮጵያ አንድነት” thesis (አዳፍኔ) እና እንደ ኢህአዴግ ዘመን የብሄር መብቶች መከበር ወይም መቀንቀን የበዛበት ፌዴራላዊት ኢትዮጵያ አንድነት anti-thesis (ዘርዝሬ) አንጻር፣ አማካይ ቦታን የሚይዝ (በሁለቱ መሃል የሚሆን) synthesis (መንዝሬ) ይሆናል ባይ ነው ዳንኤል። Thesis—anti-thesis—Synthesis: አዳፍኔ—ዘርዝሬ— መንዝሬ!
በዚህም የጃፓንና የፈረንሳይን የሃገር ግንባታ ስኬት እንደምሳሌ በመውሰድ፣ የብልጽግናው አገዛዝ “ታላቁ ትርክት” ምን ዓይነት ሃገር መንግስት እንደሚያልም ያመላክታል መጽሐፉ (ገጽ 530-31)።
ጸሃፉው ምንም እንኳን “ታላቁ ትርክት” መገንባትና መቆም ያለበት ሌሎች ተወዳዳድሪ ወይም ተገዳዳሪ ትርክቶችን በማጣጣልና በማጥቃት መሆን እንደሌለበት የሚገልጽ ቢሆንም ቅሉ፣ የመጽሐፉ 325 ገጾች ያህል ማለትም 56.5 በመቶውን ተቃራኒ ትርክቶች ብሎ የፈረጃቸውን የኦነግ፣ የህወሓት፣ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴንና የጃውሳ ትርክቶች ያላቸውን በጠላትነት ጭምር ፈርጆ ለማጥቃት አውሎታል። ይሄም የመጽሐፉ አንደኛው ታላቁ ተቃርኖ ሆኖ ይታያል።
መጽሐፉ ሌላም ትልቅ ተቃርኖ ይታይበታል። ምንም እንኳን መፍጠር የሚፈለገው አዲሱ “ታላቁ ትርክት” የሌሎች ሁለት ተቃራኒ ትርክቶች (thesis vs anti-thesis) ምንዛሬ (synthesis) ነው ብሎ ቢነሳም፣ የመጽሐፉ ዋና ጭብጥ የሚያመላክተው ሃቅ ግን “ታላቅ” የተባለው ትርክት ከሁለቱ ተጻራሪ ትርክቶች አንደኛውን ትርክት ማለትም የአዳፍኔን ትርክት (the thesis) ከሞላ ጎደል እንዳለ የወሰደ (espouse ያደረገ) መሆኑን ነው። ለምሳሌ ኦሮሞን ወደ ጎሳዎች ስብስብ ደረጃ አውርዶ ብቻ እውቅና ለመስጠት የሚደዳው ያጼው ወይም የደርግ ዘመን የኢትዮጵያ ሃገረ መንግስት ትርክትና የታሪክ ትንተና ከሞላ ጎደል በዚህ መጽሐፍ ከቀረበው እምብዛም ልዩነት ያለው አለመሆኑ ለዚህ ማሳያ ነው። ይሄ የታሪክ ትንተና ምንጩ፣ ያጤዎቹ ዘመን ሊህቃን የታሪክ እይታ መሆኑ ይታወቃል። እናም እንዴት ሆኖ ነው አዲስ synthesis የሚሆነው ይሄ ትርክት? ትርክቱ የብልጽግናው አዲሱ ጠጅ ባጤዊቹ አሮጌ አቁማዳ የቀረበ ነው ቢባል ልክ ሊሆን ይችላል።
5) ዳንኤል ክብረት እንደ ተክለጻዲቅ መኩሪያ
የባለ ዝቅተኛና መካከለኛ መዓረግ ወታደሮች ስብስብ የነበረው ደርግ በኮለኔል ፍሰሃ ደስታ መጽሐፍ ላይ ይመስለኛል እንደተገለጸው፣ “የኢትዮጵያ መንግስት በትረ ስልጣን ከነዘውዷ መሬት ላይ ወድቃ አገኘናት፣ ታሪክም ሃገር እንድንመራ ሃላፊነት ጣለብን” በሚል ሸፍጥ፣ የ1974ቱን ህዝባዊ አብዮት ጠልፎ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ፣ ልክ ዛሬ ብልጽግና እንደሚያደርገው አዲስ የሀገረ መንግስት ትርክት መፍጠር እንዳለበት ወሰነ።
በፊውዳል አጤዎቹ ዘመን ”የይሁዲው ሰሎሞን ዘር” ትርክት መቀጠል እንደማይችሉ ገብቷቸዋል ወታደሮቹ። እና እንዴት ይደረግ ሲባል፣ ከሽፍትነት ተነስቶ የክርስቲያን አቢሲኒያ ንጉስ መሆን የቻለውንና፣ የዘር ሃረጉም ከሰለሞን ዘር ውጭ መሆን ብቻም ሳይሆን ማህበራዊ መሰረቱም ልክ እንዳብዛኛዎቹ የደርግ ወታደሮች ከደሃው ወገን የሆነውን አጼ ቴውድሮስን መሰረት ያደረገ የኢትዮጵያ ታሪክና ትርክት በመፍጠር ህዝቡ ውስጥ እንዲሰርጽ ማድረግ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ይስማማሉ የደርጉ ዋና ዋና ሰዎች (ቴድሮስ እናቱ ጉልት ሻጭ ነበረች ይባላል)።
የደርጉ ሁነኛ ሰው የነበረው ሻምበር ፍቅረ ስላሴ ወግደረስም እንደሚለው፣ ለዚህ የትርክት ፈጠራ ፕሮጀክት አቶ ተክለጻዲቅ መኩሪያን መልምሎ፣ ‘ሎንዶንን’ ጨምሮ በሌሎች ያውሮፓ ሃገሮች ወዳሉ ቤተ መጽሐፍት ድረስ ሄዶ የቴውድሮስን ታሪክ እንዲጽፍ ከመንግስት ካዝና በጀት የመደበው ራሱ ነበር። በዚሁ መሰረት ተክለጻዲቅ መኩሪያ ታሪኩን ጽፎ ሲያበቅ፣ ከህትመት በፊት ያለውን ረቂቅ ሻምበሉ እንዲያየው ይሰጠዋል። በውነቱ ከዚህ በኋላ ሆነ የሚባለው አስገራሚ ነገር ነበር ማለት ይቻላል…
ተክለጻዲቅ መኩሪያ በዛ የመጽሐፉ ረቂቅ ማድረግ የሞከርው፣ ስለቴውድሮስ ወደ እውነታው የተጠጋውን ታሪክ ከሰነዶችም ሆነ ከማህበረሰቡ ትውስታዎች ያገኘውን እንዳለ ማስቀመጥ ነበር። ቴውድሮስ ከሽፍትነት ተነስቶ ፋሽስታዊ ባህሪን ጭምር ያዳበረ ጨካኝና ጨፍጫፊ መሪ እንደነበር፤ የሰው ልጆችን ጎጆ ውስጥ አስገብቶ የማቃጠልን ጨምሮ የማረካቸው የወሎ ኦሮሞ ተዋጊዎችን ከነነፍሳቸው ወደ ገደል በመወርወር እንደቲማቲም ፈርጠው እንዲሞቱ ሁሉ ያደርግ እንደነበር፣ እጅና እግር መቁረጥና ሌሎች መሰል የሽብር ድርጊቶችን በንጹሃን ሰዎች ላይ ጭምር ይፈጽም እንደነበረ…ወዘተ ዘግቦ ነበር ያቀረበው አቶ ተክለጻዲቅ መኩሪያ።
ሻምበል ፍቅረስላሴ እንደሚለው፣ የመጽሐፉን የመጀመሪያ ረቂቅ ካነበበ በኋላ አቶ ተክለጻዲቅን አስጠርቶ ይሄ የተጻፈው ታሪክ ፍጹም ተቀባይነት እንደሌለውና ሌላ ለደርጉ መንግስት የሚጠቅም ዓይነት ታሪክ እንደገና ጽፎ እንዲያመጣ ያዘዘው ሲሆን፣ “የታሪክ ጸሃፍው” ተክለጻድቅ መኩሪያም ይሄንኑ ‘ታሪካዊ ትዕዛዝ’ ተቀብሎ በመፈጸም፣ የቴውድሮስን ታሪክ ደርግ በሚፈልገው መልኩ ጽፎት መጽሐፉም ታትሟል። አንዳንዶቹ የቴውድሮስ ፋሽስታዊ ጭካኔዎችም “የኢትዮጵያን አንድነት ለመገንባት የተደረጉ ናቸው” በሚል ለዝበው እንዲቀርቡ ተደርጓል።
የደርግ መንግስትም ይሄ “የቴውድሮስ ታሪክ” ፈጠራ እነሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ጭምር በሚመሯቸውና ባማርኛ ቋንቋ በሚሰሩ ፕሮፓጋንዳዊ ትያትሮች፣ በስነጽሁፎች፣ በኪነትና ሙዚቃ፣ በድራማዎችና ፖለቲካዊ ድስኩሮች ጭምር ተጠቅሞ ህዝቡ ውስጥ ለማስረጽ ብዙ ጥረት ተደርጓል በዘመኑ። ይሄ የደርግ መንግስት የፈጠረው አጤ ቴውድሮስ ላይ የተንጠለጠልው የኢትዮጵያ አንድነት ትርክት ተጽኖ፣ ዛሬም ድረስ በተለይም ባማርኛ ቋንቋ በሚጻፉ የታሪክ ድርሰቶችና ሙዚቃን ጨምሮ በሌሎችም የኪነጥበብ ስራዎች ውስጥ ሲንጸባረቅ ይታያል። በዚህ ረገድ የነ ቴዲ አፍሮ፣ ማዲንጎ አፎወርቂና ሌሎች የዘመኑ ተጽኖ ፈጣሪ የፕሮፓጋንዳ ዘፈኖችን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። በዚሁ ምክንያት ይመስላል አብዱልጀሊል የተባለ ወጣት ጸሃፊ ስለቴውድሮስ ያሳተመውን አንድ መጽሐፉን “ኪነት ያገነነው አጼ” የሚል ተንኳሽ ርዕስ የሰጠው።
ይሄን መጽሐፍ አንብቤ ከጭረስኩ በኋላ በተለይም የመጽሐፉ ምረቃ ላይ የተገኙ የመንግስት ባለስልጣናትን ሳስታውስ የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር፣ ዳንኤል እዚ ላይ ለመጫወት የሞከረው ሚና፣ የደርጉን ዘመን ጸሃፊ የተክለጻዲቅ መኩሪያን ሚና ሆኖ ታይቶኛል። ይኸውም ልክ እንደደርግ ሁሉ ህዝባዊ ትግልን ነጥቆ ስልጣን ላይ የወጣውን የብልጽግና አገዛዝን ለማጽናት አዲስ የፈጠራ ታሪክና ትርክት ለማዋቀር መሞከር። ከዛም መንግስት በሚቆጣጠራቸውም ሆነ ከአገዛዙ ጋር ቅርበት ባላቸው የሚዲያ፣ የሙዚቃ፣ የትያትርና የሌሎች ዓይነት ፕላትፎርሞች ተጠቅሞ ትርክቱን ህዝብ ውስጥ ለማስረጽ መሞከር።
የደርጉ ዘመን ውጥን ብዙም አልተሳካም ማለት ይቻላል። ይሄኛው የብልጽግና አገዛዝ ሙከራስ ይሳካ ይሆን? አብረን የምናየው ነው የሚሆነው፡፡
6) ማጠቃለያ
ሲጠቃለል፣ ጸሐፊው ሊፈጥረው የሚታትረው የብልጽግና አገዛዝ “ታላቁ ትርክት” ዋናው መሰረቱ በገጽ 372-512 ላይ ያስቀመጣቸው የኢትዮጵያ ታሪክ አተያይ ላይ መሆኑ ግልጽ ነው። በዚህ ምክንያት ትርክቱ ሁለት አበይት ተግዳሮቶች ሊገጥሙት ይችላሉ የሚል ግምት አለኝ።
አንደኛ፥ አዲስ ነው ተብሎ የሚፈጠረው ትርክት፣ በርግጥም አዲስ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ያው “ኢትዮጵያዊያን ተቀላቅለናል፣ ተጋብተናል ተዋልደናል፣ ያንድ ብሄር የሆነ ቋንቋ እንጂ መሬት ወይም ስልጣኔ የለም” …. ወዘተ በሚል የቆየና የደከመ የታሪክ ትንተና (ዶር ሳራ ማርዛጎራ የተባለች የታሪክ ተመራማሪ “ታላቁ ተረት—The Great Tradition” ትለዋለች ይሄንን) ላይ የቆመው የዳንኤል ክብረት ‘ታላቁ ትርክት’፣ ያንኑ ገልብጦ በማምጣት እንዳዲስ የማቅረብ ነገር ስለሆነ ስኬት ለማስመዝገብ ሊቸገር ይችላል።
ሁለተኛውና ዋናው ተግዳሮት ግን፣ ይሄ የታላቁ ትርክት መሰረት ይሆናል የተባለው የኢትዮጵያ ታሪክ አጠናንና አተያይ፣ ሃብታሙ አለባቸው መሰረታዊ የስነ ዘዴ ግድፈት (fundamental methodological flaw) የሚለው ከባድ ችግር ሰለባ የመሆኑ እውነታ ነው። ይሄውም የዘመናዊት ኢትዮጵያን ታሪክ ከክርስቲያን ፊውዳል አቢሲኒያ ታሪክ ጋር አንድ ላይ ጨፍልቆ በማቅረብ፣ ሁለቱ የፖለቲካ ስሪቶች (the two political entities) አንድና ያው (one and the same) እንደሆኑ አድርጎ ማቅረብ ነው። ዳንኤል ክብረት በዚህ መጽሐፍ ውስጥ (በሌሎቹም እንዲሁ) ይሄን ሳይንሳዊ ግድፈት በሰፊው ሲፈጽም ይታያል። በዚህም ምክንያት የሚፈጠረው ታላቁ ትርክት ምናልባትም ታላቁን ተቃርኖ ሊያዋልድ ይችላል።
Editor’s Note: The opinions expressed in the articles published on UMD Media are solely those of the individual authors and do not necessarily reflect the views or opinions of the editorial team or UMD Media as an organization. The publication of any opinion piece does not imply endorsement or agreement by UMD Media. Readers are encouraged to critically evaluate the content and form their own conclusions. Leave your comments below. Send us your thoughts and reflections to umd.media.2020 at gmail dot com.
Guidelines for contributors All contributions and comments submitted to UMD Media must adhere to the following guidelines. Respectful Language: Avoid using ethnic adjectives that generalize or portray an entire ethnic group in a negative light. Such language is harmful, divisive, and contrary to our commitment to fostering a respectful and inclusive environment. No Incitement: Content that incites hatred, violence, or discrimination against any individual or group based on ethnicity, race, religion, etc will not be tolerated. Constructive Dialogue: We encourage constructive dialogue and the sharing of diverse perspectives. However, it is essential to express opinions in a manner that respects the dignity and humanity of all individuals and groups. Moderation and Enforcement: Our editorial team reserves the right to moderate and, if necessary, remove any content that violates these guidelines. Repeat offenders may be subject to account suspension or banning. By contributing to our platform, you agree to abide by these guidelines and help us maintain a respectful and inclusive community.
Subscribe to UMD Media channel. Join UMD Media Telegram Channel: https://t.me/UMDMedia
የአንተ ስህተቶች እና ተቃርኖዎች
1/ “የሽፋን ገጽ ላይ የተቀመጠው መሸጫ ዋጋ፥ ብር 1000” ብለህ መልሰህ ደግሞ “አንዳንድ ወዳጆቼ “አባጫብሳ አንተ ሞኝ ነህ እንዴ የዳንኤል ክብረትን መጽሐፍ በ1300 ብር ገዝተህ የምታነበው…ገንዘብና ጊዜ ተረፈህ እንዴ?” ” ትለለህ
2/ “አቶ ተክለጻዲቅን…” ጸሐፌ ትእዛዝ የሚለውን ማዕረግ ሆን ብለህ ለማጣጣል ትሞክራለህ፤ ስለዚህ ያንተን ሃተታ ለመዝለቅ አልችልም፡፡ ምንም እንኳ የዳኔልን መጽሃፍ ባልወደውም ቅሉ አንተም አጻጻፍህ በተሳሳተና በተጽእኖ ስር የወደቀ በመሆኑ የማንበብ ፍላጎቴን ዘግተኸዋል